መልስ - ሱረቱል ሁመዛህ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት። 1 * ለዚያ ገንዘብን የሰበሰበና የቆጣጠረው (ያደለበውም) ለሆነ ፤(ወዮለት)። 2 * ገንዘቡ የሚያዘወትረው መሆኑን ያስባል። 3 * ይከልከል፤ በሰባሪይቱ (እሳት) ውስጥ በእርግጥ ይጣላል። 4 * ሰባሪይቱም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 5 * የተነደደችው የአላህ እሳት ናት። 6 * ያቺ በልቦች ላይ የምትዘልቅ የሆነችው። 7 * እርሷ በእርግጥ በእነርሱ ላይ የተዘጋጀች ናት። 8 * በተዘረጋች አዕማድ ውስጥ (የተዘጋች ናት)። 9 [ሱረቱ አል-ሁመዛህ: 1-9]
ተፍሲር፡
1- {ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት። 1} ሰዎችን አብዝቶ ለሚያማ እና ለሚዘልፍ ሰው የመከራ እና የስቃይ ቅጣት አለበት።
2- {ለዚያ ገንዘብን የሰበሰበና የቆጣጠረው (ያደለበውም) ለሆነ ፤(ወዮለት)። 2} ለዛ ገንዘብ ከመሰብሰብና ከመቁጠር ውጭ ሌላ ሀሳብ ለሌለው ወዮለት።
3- {ገንዘቡ የሚያዘወትረው መሆኑን ያስባል። 3} የሰበሰበው ገንዘብ ከሞት ያድነዉና በዱንያ ህይወትም የሚያዘወትረው ይመስለዋል።
4- {ይከልከል፤ በሰባሪይቱ (እሳት) ውስጥ በእርግጥ ይጣላል። 4} ጉዳዩ ይህ አላዋቂ እንዳሰበው አይደለም። ይልቁን ከከባድነቷ አንፃር የተወረወረላትን ሁሉ የምትፈጭና የምትሰባብር ወደሆነችው የጀሀነም እሳት ይወረወራል።
5- {ሰባሪይቱም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 5} የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህች የተጣለላትን ሁሉ የምትፈጨው እሳት ምንነት ምን አሳወቀህ?!
6- {የተነደደችው የአላህ እሳት ናት። 6} እርሷ የምትቀጣጠል የአላህ እሳት ነች።
7- {ያቺ በልቦች ላይ የምትዘልቅ የሆነችው። 7} በሰዎች አካል ወደ ልባቸው ዘልቃ የምትገባ ነች።
8- {እርሷ በእርግጥ በእነርሱ ላይ የተዘጋጀች ናት። 8} በውስጧ ለሚሰቃዩባትም የምትቆለፍባቸው ነች።
9- {በተዘረጋች አዕማድ ውስጥ (የተዘጋች ናት)። 9} ከውስጧም እንዳይወጡ በተዘረጉ ረዣዥም አዕማድ የተዘጋች ነች።