መልስ- ሱረቱ ተካሡር እና ተፍሲሩ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በብዛት መፎካከር (ጌታችሁን ከመገዛት) አዘነጋችሁ። 1 * መቃብሮችን እስከ ጎበኛችሁ ድረስ። 2 * ተከልከሉ፤ ወደፊት (ውጤቱን) ታውቃላችሁ። 3 * ከዚያም ተከልከሉ፤ ወደ ፊት ታውቃላችሁ። 4 * በእውነቱ (የሚጠብቃችሁን) እርግጠኛ ዕውቀትን ብታውቁ ኖሮ፤ (ባልዘናጋችሁ ነበር)። 5 * ገሀነምን በርግጥ ታያላችሁ። 6 * ከዚያም እርግጠኛን ማየት ታዩዋታላችሁ። 7 * ከዚያም ከድሎታችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ። 8} [ሱረቱ ተካሡር: 1-8]
ተፍሲር፡
1- {"{በብዛት መፎካከር (ጌታችሁን ከመገዛት) አዘነጋችሁ። 1"} ሰዎች ሆይ! በገንዘብና በልጆች መፎካከራችሁ አላህን ከመገዛት አዘነጋችሁ።
2- {"መቃብሮችን እስከ ጎበኛችሁ ድረስ። 2"} ሞታችሁ ወደ መቃብራችሁ እስክትገቡ ድረስ አዘነጋችሁ።
3- {"ተከልከሉ፤ ወደፊት (ውጤቱን) ታውቃላችሁ። 3"} በእርሷ መፎካከራችሁ አላህን ከመታዘዝ ሊያዘናጋችሁ የሚገባ አይደለም። የዚህ መዘናጋታችሁ መጨረሻውን ታዩታላችሁ።
4- {"ከዚያም ተከልከሉ፤ ወደ ፊት ታውቃላችሁ። 4"} አሁንም ፍፃሜውን ታውቃላችሁ።
5- {"በእውነቱ (የሚጠብቃችሁን) እርግጠኛ ዕውቀትን ብታውቁ ኖሮ፤ (ባልዘናጋችሁ ነበር)። 5"} በእርግጥ ወደ አላህ ተመላሾች መሆናችሁንና በሥራችሁንም እንደሚመነዳችሁ በእርግጠኝነት ብታውቁ ኖሮ በገንዘብና በልጆች መፎካከር ላይ አትጠመዱም ነበር።
6- {"ገሀነምን በርግጥ ታያላችሁ። 6"} በመሀላ አስረግጨ እናገራለሁ በእለተ ትንሣኤ እሳትን ትመለከታላችሁ።
7- {"ከዚያም እርግጠኛን ማየት ታዩዋታላችሁ። 7"} ከዚያም ያለምንም ጥርጥር በተጨባጭ ትመለከቷታላችሁ።
8- {"ከዚያም ከድሎታችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ። 8"} ከዚያም አላህ በዚያን ቀን ከጤናም ከሀብትም ከሌሎችም ፀጋዎች በኩል ስለዋለላችሁ ውለታ ይጠይቃችኋል።