ጥ 2፡ ሱረቱል ዘልዘላን ቅራና ተፍሲሩን አስቀምጥ?

መልስ- ሱረቱል ዘልዘላህ እና ተፍሲሩ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።

{ምድር (በኀይል) መንቀጥቀጥዋን በተንቀጠቀጠች ጊዜ፤ 1 * ምድር ሸክሞችዋን ባወጣችም ጊዜ፤ 2 * ሰውም ምን ሆነች? ባለ ጊዜ፤ 3 * በዚያ ቀን ወሬዎችዋን ትናገራለች። 4 * ጌታህ ለእርሷ በማሳወቁ ምክንያት። 5 * በዚያ ቀን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) እንዲያዩ ይደረጉ ዘንድ (እንደየሥራቸው) የተለያዩ ሆነው (ከመቆሚያው ስፍራ) ይመለሳሉ። 6 * የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 7 * የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 8} [ሱረቱ-ዘልዘላህ፡ 1-8]

ተፍሲር፡

1- {ምድር (በኀይል) መንቀጥቀጥዋን በተንቀጠቀጠች ጊዜ፤ 1} ማለትም በዕለተ ትንሳኤ ከሚደርስባት ከባድ እንቅስቃሴ አንፃር ምድር በተንቀጠቀጠች ጊዜ።

2- {"ምድር ሸክሞችዋን ባወጣችም ጊዜ፤ 2"} ማለትም ምድር በሆዷ ውስጥ ያለውን ሙታንም ሌላውንም ባወጣች ጊዜ።

3- {"ሰውም ምን ሆነች? ባለ ጊዜ፤ 3"} የሰው ልጅ ግራ ተጋብቶ "ምድር ምን ነክቷት ነው የምትንቀጠቀጠውና የምትናወጠው?!" ይላል።

4- {"በዚያ ቀን ወሬዎችዋን ትናገራለች። 4"} በዚያ ከባድ ቀን ምድር እርሷ ላይ የተደረገውን መልካምና ክፉውን ሁሉ ምድሪቱ ትዘከዝከዋለች።

5- {"ጌታህ ለእርሷ በማሳወቁ ምክንያት። 5"} ምክንያቱም አላህ ስላሳወቃትና እንድትናገርም ስላዘዛት ነው።

6- {"በዚያ ቀን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) እንዲያዩ ይደረጉ ዘንድ (እንደየሥራቸው) የተለያዩ ሆነው (ከመቆሚያው ስፍራ) ይመለሳሉ። 6"} በዚያ ምድሪቱ በምትናወጥበት ከባድ ቀን ሰዎች በዱኒያ ሳሉ የሰሩትን ሊመለከቱ ቡድን ቡድን እየሆኑ ወደ መተሳሰቢያው መስክ ይወጣሉ።

7- {"የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 7"} በመሆኑም የትንሿን ትንኝ ክብደት ያህል እንኳ በጎ የሰራ ሰው ስራውን ፊት ለፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል።

8- {"የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 8"} በሷው ክብደት ልክ ክፉ ሥራ የሠራም ሰው እንዲሁ ስራውን ፊት ለፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል።