መልስ - ሱረቱል ማዑን እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) 1 * ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ 2 * ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው። 3 * ለሚሰግዱ ወዮላቸው፤ 4 * ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)። 5 * ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለሆኑት። 6 * የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለሆኑት (ወዮላቸው)። 7} [ሱረቱ አል'ማዑን 1-7]
ተፍሲር፡
1- {ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) 1} የትንሣኤ ቀን ምንዳን ያስተባበለውን አወቅከውን?
2- {ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ 2} ያ ወላጅ አልባን ከጉዳዩ በኋይል የሚገፈትረው ነው።
3- {ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው። 3} ራሱንም ይሁን ሌሎች ድሆችን እንዲመግቡ አያነሳሳም።
4- {ለሚሰግዱ ወዮላቸው፤ 4} ጣፋትና ስቃይ ለሰጋጆች ሆነ።
5- {ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለሆኑት፤ (ሰጋጆች)። 5} ለነዚያ ምንም ሳያሳስባቸው በሶላታቸው ለሚቀልዱት ሰጋጆች ሆነ።
6- {ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለሆኑት። 6} ለነዚያ ሰላታቸውና ሥራዎቻቸው ለይዩልኝ ይስሙልኝ ለሆኑ፤ ለአላህም ብለው ኢኽላሳቸውን ለማያጠሩ ሰዎች ሆነ።
7- {የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለሆኑት (ወዮላቸው)። 7} እናም ሌሎችን ቢረዱበት ምንም ጉዳት በማይደርስባቸው ጉዳይም ሌሎችን ከመርዳት የሚታቀቡ ለሆኑት ወዮላቸው።