መልስ- የሰላት አፈጻጸም፦
1- ሳይዛነፉና ሳይዟዟሩ ሙሉ አካልን ወደ ቂብላ (ማዞር) መቅጣጨት፤
2- ከዚያም በልቡ ሊሰግደው የፈለገውን ሰላት በቃል መናገር ሳይጠበቅበት በውጡ ማሰብ፤
3 - ከዚያም "አሏሁ አክበር!" ብሎ ተክቢረተል ኢሕራም ማድረግ፤ ተክቢራውን በሚልበት ጊዜ እጅን በትከሻ ትይዩ ማንሳት፤
4- ከዚያም የቀኝ እጅን መዳፍ በግራ እጅ የመዳፍ ጀርባ ላይ አጣምሮ ደረት ላይ ማስቀመጥ፤
5- ከዚያም እንዲህ ብሎ ዱዓኡል ኢስቲፍታሕን ማለት፦ "አላሁመ ባዒድ በይኒ ወበይነ ኸጧያየ ከማ ባዐድተ በይነል-መሽሪቂ ወል-መግሪቢ አሏሁመ ነቂኒ ሚን ኸጧያየ ከማ ዩነቀ-ሥ-ሠውቡል አብየዱ ሚነ ደነስ አላሁመ 'ግሲልኒ ሚን ኸጧያየ ቢሥ-ሠልጂ ወልማኢ ወል-በረድ" ትርጉሙ፦ "አላህ ሆይ! በምሥራቅና በምዕራብ መካከል እንዳራራቅከው እኔንም ከወንጀሌ አርቀኝ፤ አላህ ሆይ! ነጭ ልብስ ከቆሻሻዎች እንደሚጸዳው እኔንም ከወንጀሌ አጥራኝ፤ አላህ ሆይ! እኔን ከወንጀሌ በውሃ እና በፈሳሹም በደረቁም በረዶ እጠበኝ።"
ወይም እንዲህ ይበል: "ሱብሓነከ አልላሁምመ ረበና ወ ቢሐምዲከ ወተባረከ ኢስሙከ ወተዓላ ጀዱከ ወላኢላሃ ገይሩክ" ትርጉሙ፦ "ጥራት ይገባህ አላህ ሆይ! ምስጋናም ላንተ ነው። ስምህ ከፍ ያለ ግርማህም የላቀ ነው፤ ካንተም በቀር አምላክ የለም።"
6- ከዚያም እንዲህ በማለት በአላህ ይጠበቅ፦ "አዑዙ ቢላሂ ሚነ ሸይጧኒ-ር-ሯጂም" ትርጉሙ፦ "ከተረገመው ሰይጣን በአላህ እጠበቃለሁ።" 7- ከዚያም ቢስሚላህ ካለ በኋላ ፋቲሓን እንዲህ ብሎ ያንብብ፦ «ቢስሚልላሂ‐ር‐ረሕማኒ‐ር‐ረሒም» [ትርጉሙ፡ በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው] (1) «አልሓምዱ ሊልላሂ ረቢል ዓለሚን» (ትርጉሙ: ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የተገባው ነው) (2) «አርረሕማን አርረሒም» (ትርጉሙም: እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው) (3) «ማሊኪ የውሚ-ድ-ዲን» (ትርጉሙ: የፍርዱ ቀን ባለቤት ለሆነው።) (4) «ኢይያከ ነዕቡዱ ወኢይያከ ነሰተዒን» (ትርጉሙ: አንተን ብቻ እንገዛለን አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምንሃለን) (5) «ኢህዲና‐ስ‐ሲሯጦል ሙስተቂም» (ትርጉሙም: ቀጥተኛውን መንገድ ምራን) (6) «ሲሯጦ‐ል‐ለዚነ አንዓምተ ዓለይሂም ገይሪል መግዱቢ ዓለይሂም ወለድ-ዷሊን» (ትርጉሙም: የእነዚያ ፀጋህን የዋልክላቸውን ሰዎች መንገድ በነዚያ የተቆጣህባቸውን እና የተሳሳቱትንም አይደሉም።) (7) [አል'ፋቲሓ፡ 1-7]
ከዚያም «አሚን» ይበል፤ ትርጉሙም አላህ ሆይ! ዱዓችንን ተቀበለን ማለት ነው።
8 - ከዚያም የገራለትን ቁርአን ይቅራ፤ የሱብሒን ሰላት ቁርኣን ንባብ ማርዘሙ መልካም ነው።
9 - ከዚያም ሩኩዕ ያደርጋል፡ ማለትም አላህን በማላቅ ይጎነበሳል። ወደ ሩኩዕ ሲወርድም ሁለት እጆቹን በትከሻው ትይዩ አድርጎ "አሏሁ አክበር" እያለ ይወርዳል። የአኳኋኑ ሁኔታ ሱና፦ ጀርባውን ለጥ አድርጎ ጭንቅላቱንም በጀርባው ልክ አስተካክሎ የሁለት እጆቹ ጣቶችን ለያይቶ ጉልበቱን መያዝ ነው።
10 - በሩኩዑ ጊዜ ሶስት ጊዜ እንዲህ ይበል፡ "ሱብሓነ ረቢየል ዓዚም" (ትርጉሙም፡ ጥራት ይገባህ ታላቁ ጌታየ)፤ "ሱብሓነከሏሁመ ወቢሓምዲከ አሏሁግፊርሊ" (ትርጉሙም፡ ጥራት ይገባህ ምስጋናም ላንተው ነው፤ መሀርታህን ለግሰኝ።) ቢል በላጭ ነው።
11 - ከዚያም ከሩኩዕ ሁለት እጆቹን በትከሻው ትይዩ አድርጎ እንዲህ እያለ ቀና ይበል፡ "ሰሚዐልላሁ ሊመን ሐሚደህ" (ትርጉሙም፡ አላህ የሚያመሰግኑትን ሰሚ ነው።) ኢማሙን ተከትሎ የሚሰግድ "ሰሚዐሏሁ ሊመን ሐሚደህ" ሳይሆን "ረበና ወለከል ሓምድ" (ትርጉሙም፡ ጌታችን ሆይ! ምስጋናም ላንተ ነው።) ነው የሚለው።
12 - ከዚያም ቀና ካለ በኋላ እንዲህ ይበል፡ "ረበና ወለከል ሐምድ ሚልኡ ሰማዋቲ ወል አርዲ ወሚልኡ ማሺእተ ሚን ሸይኢን ባዕዱ" (ትርጉሙም፡ ጌታችን ሆይ! ምስጋና በሰማያትና በምድር ሙሉ ላንተ ይሁን፤ ከዚያም በኋላ አንተ በምትሻው ነገር ሙሉም ላንተ ይሁን።)
13 - ከዚያም ለመጀመርያው ሱጁድ እንዲህ እያለ ይወርዳል፡ "አሏሁ አክበር"፤ ሱጁድ የሚያደርገውም በሰባት የሱጁድ አካላቱ ሲሆን እነርሱም፡ ግንባር አፍንጫን ጨምሮ ፣ ሁለት መዳፎች፣ ሁለት ጉልበቶቹ እና የእግር ጫፎች ናቸው። አካላቱን ከጎኑ ያርቃቸው፤ ክርኖቹንም ምድር ላይ አያንጥፋቸው፤ በእግሩ ጫፍም (በጣቶቹ) ወደ ቂብላ ይቅጣጭ።
14 - በሱጁዱም ወቅት ሶስት ጊዜ እንዲህ ይበል፦ "ሱብሓነ ረቢየል አዕላ" (ትርጉሙም፡ ከፍ ያልከው ጌታየ ሆይ! ጥራት ይገባህ።) እንዲህ ብሎ ቢጨምር ደግሞ ይበልጥ የተሻለ ነው፡ "ሱብሓነከሏሁምመ ረብበና ወቢሓምዲከ አሏሁምመግፊርሊ" (ትርጉሙም፡ ጥራት ይገባህ ምስጋናም ላንተ ነው ጌታየ! መሀርታህን ለግሰኝ።)
15 - ከዚያም ከሱጁድ "አሏሁ አክበር" እያለ ቀና ይበል።
16 - ከዚያም በሁለቱ ሱጁዶች መካከል የቀኝ እግሩን ተረከዝ ተክሎ በግራ እግሩ የውስጠኛው ክፍል ላይ ይቀመጥ። የቀኝ እጁን በቀኝ ታፋው ላይ አድርጎ ወደ ጉልበቶቹ አስጠግቶ ያስቀምጣቸው። ትንሿን ጣቱንና የቀለበት ጣቱን አጥፎ ጠቋሚ ጣቱን በዱዓእ ጊዜ ያንቀሳቅስ። የአውራ ጣቱን ጫፍም ከመሀል ጣቱ ጫፍ ጋር አድርጎ እንደ ክብ ነገር ይስራባቸው። የግራ እጁን ደግሞ ጣቶቹን ዘርግቶ በግራ ታፋው ላይ ወደ ጉልበቱ አስጠግቶ ያስቀምጠው።
17 - በሁለቱ ሱጁዶች መካከል ሲቀመጥ እንዲህ ይበል፦ “ረቢግፊርሊ ወርሐምኒ ወህዲኒ ወርዙቅኒ ወጅቡርኒ ወዓፊኒ” ትርጉሙ፡ "አላህ ሆይ ይቅር በለኝ ማረኝ ምራኝ ፣ ደግፈኝ ፣ ጠብቀኝ፣ ስጠኝ፣ ከፍም አድርገኝ።"
18 - ሁለተኛውንም ሱጁድ ንግግሩንም ተግባሩንም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ልክ እንደመጀመርያው ያድርግ። ወደ ሱጁድ በሚወርድበትም ጊዜ "አሏሁ አክበር" ይበል።
19 - ከዚያም ከሁለተኛው ሱጁድ "አሏሁ አክበር" እያለ ቀና ይበል። የሁለተኛውንም ረከዓህ ንግግሩንም ተግባሩንም ልክ በመጀመርያው ረከዓህ እንዳደረገው ያድርግ። ነገር ግን የመክፈቻ ዱዓ አያደርግም።
20 - ከዚያም ሁለተኛውንም ረከዓህ እንዳጠናቀቀ "አሏሁ አክበር" እያለ ቀና ይበልና በሁለቱ ሱጁዶች መካከል እንደተቀመጠው ሆኖ ይቀመጥ።
21 - በዚሁ በተቀመጠበት በሚከተለው መልኩ ተሸሁድን ያነባል፡ “አትተሒያቱ ሊላሂ ወስሶላዋቱ ወጥጠይባቱ ፣ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካትሁ ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ። አልላሁምመ ሰልሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመዲን ከማ ሶልለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ። አልላሁምመ ባሪክ ዓላ ሙሐመዲን ወዐላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ወዓላ አሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ። አሏሁማ ኢኒ አዑዙ ቢከ ሚን ዐዛቢል-ቀብሪ ወሚን ዐዛቢ ጀሀነም ወ ሚን ፊቲነቲል-መሕያ ወል-መማቲ ወ ሚን ሸር-ሪ ፊቲናቲል መሲሒ-ድ-ደጃል” ትርጉም ፡- “ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን ፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን ፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ ፤ ሙሐመድም የአላህ አገልጋይና መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ፤ አላህ ሆይ! ውዳሴህን ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸው አውርድላቸው፤ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና።አላህ ሆይ! ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው ረድዔትን እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸውም ረድዔትን አውርድላቸው። አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና። አላህ ሆይ! ከቀብር ፈተና፣ ከጀሀነም ፈተና፣ ከህይወትና ሞት ፈተናዎች እንዲሁም ከመሲሒ ደጃልም ፈተና ክፋት በአንተ እጠበቃለሁ።" ከዚያም ከቅርቢቱ ዓለምና ከመጨረሻው ዓለም የፈለገውን መልካም ነገር በዱዓእ አላህን ይማፀናል።
22 - ከዚያም ወደ ቀኝ እየዞረ እንዲህ ብሎ ያሰላምት "አሰላሙ ዓለይኩም ወራሕመቱሏህ"፤ ወደ ግራ እየዞረም እንዲሁ ይበል።
23 - ሶላቱ ሶስት ረከዓ ወይም አራት ረከዓህ የሚሰገድበት ከሆነ ደግሞ ተሸሁድ ማለትም "አሽሀዱ አን ላ ኢላሃ ኢለሏህ ወአሽሀዱ አነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉህ" የሚለው ድረስ ካለ በኋላ የቀረውን ረከዓ ለመቀጠል ይቆማል።
24 - ከዚያም "አሏሁ አክበር" እያለ ይቁም እጆቹንም በትከሻው ትይዩ ከፍ ያድርጋቸው።
25 - ከዚያም ሁለተኛውን ረከዓህ በሰገደበት አኳኋን አድርጎ ሶላቱን ይቀጥል፤ ይሁን እንጂ የሚቀራው ቁርአን ፋቲሓን ብቻ ነው።
26 - ከዚያም ተወሩክ በሚባለው አኳኋኑም የቀኝ እግሩን ተረከዝ ተክሎ የግራ እግሩን ተረከዝ ደግሞ በተከለው የቀኝ እግሩ ተረከዝ ስር አሾልኮ መቀመጫውን መሬቱ ላይ ያደርጋል። እጆቹን ደግሞ ልክ በመጀመርያው ተሸሁድ ላይ እንዳደረገው አድርጎ በታፋዎቹ ላይ ያስቀመጣቸዋል።
27 - በዚሁ መቀመጡ ላይ ሙሉ ተሸሁድን ነው የሚቀራው።
28 - ከዚያም ወደ ቀኝ እየዞረ እንዲህ ብሎ ያሰላምት "አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱሏህ"፤ ወደ ግራ እየዞረም እንዲሁ ይበል።